ሕግ ማስከበርም ሆነ ማክበር አለመቻል የደቀነው አደጋ

 detention in Ethiopia
4 May 2022

by Dawit Atreso


የሕግ የበላይነትን የ11ኛ ክፍል የሲቪክ ትምህርት ምዕራፍ ሁለት በሚከተለው መንገድ ይተነትነዋል፡፡ ‹‹Rule of law means that all citizens are subject to the law and equal under the law. Law is supreme in the country. No person or government organ is above the law.›› ወደ አማርኛ ሲመለስ፣ ‹‹የሕግ የበላይነት ማለት ሁሉም ዜጋ ከሕግ በላይ አይደለም፣ እንዲሁም በሕግ ፊት እኩል ነው ማለት ሲሆን፣ ሕግ በአንድ አገር ውስጥ ፍፁም የበላይ መሆኑን ያመላክታል፡፡ በሕግ የበላይነት መርሕ መሠረት በአንድ አገር ውስጥ ማንም ዜጋም ሆነ የመንግሥት ተቋም ከሕግ በላይ አይደለም፤›› ተብሎ መተርጎም ይችላል፡፡ በተለያዩ የሕግና የፖለቲካ ትንተናዎች የሕግ የበላይነት ጽንሰ ሐሳብ ከፍ ያለ ቦታ ተሰጥቶት ይገኛል፡፡ የሕግ የበላይነት (Rule of Law) ከዴሞክራሲ መርሆዎች አንዱ ነው ተብሎም ይታሰባል፡፡ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የብዙኃን የበላይነት፣ ሰብዓዊ መብት፣ እኩልነት፣ ወዘተ እየተባሉ ከሚዘረዘሩ የዴሞክራሲ መርሆዎች አንዱ የሕግ የበላይነት መሆኑን ከበርካታ መዛግብት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ፣ ወንጀልና ሕግ አከባበር በ11ኛ ክፍል ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ክፍሎች በሲቪክስና በሌሎች ትምህርት ምዕራፎች ላይ ተደጋግመው የሚሰጡ መሠረታዊ የሕግ ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ በሥነ ሕግ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ወደ ላይም ሆነ ወደ ታች ባሉ የትምህርት እርከኖች ይነስም ይብዛ እነዚህን መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦች ትውልዱ በትምህርት እየቀሰመ የሚያድግበት ዕድል መኖሩን ከዚህ ሁኔታ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የነቃ የሕግ ግንዛቤ ያለው ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው ተብሎ በሚገመትባት ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ወቅት ሕግ ማስከበር ከባድ አደጋ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ጥያቄ ደግሞ የፍትሕ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ አወል መሐመድ፣ ችግሩ ከግንዛቤ ብቻ እንደማይመነጭ ነው የሚያስረዱት፡፡

‹‹የወንጀል መከላከል ሥራው ላይ ካሉን ሚናዎች አንዱ የወንጀል መከላከል ንቃት (ግንዛቤ) መፍጠር ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የወንጀል ግንዛቤ ወይም ንቃተ ህሊና ጉድለት ችግር ሳይሆን፣ ሆን ብሎ ሕግን የመጣስ ችግር ነው የጎላው፡፡ ወንጀሎች ብዙውን ጊዜ የሚፈጸሙት በሚገባ ዝግጅትና ቅስቀሳ እየተደረገ፣ እንዲሁም የሆነ ዓላማን ለማሳካት በማቀድ እየሆነ ነው፡፡ በየሚዲያው ሰዎችን ቀስቅሶና ልኮ የሚያስገድለው ሰው ይቅርና ታዳጊ የሚባል የስምንተኛ ክፍል ልጅም ሰውን መግደል ወንጀል እንደሆነ በደንብ ያውቃል፡፡ ሰዎችን ማፈናቀል ወንጀል መሆኑን ማንም ያውቃል፡፡ በቤተሰቡ ወይ በራሱ እንዲሆን የማይፈልገው ነገር በሌሎች ላይ ሲፈጸም ሁሉም ሊያመው መቻል አለበት፤›› ሲሉ ነው አቶ አወል የችግሩን ምንጭ የሚያስረዱት፡፡ ኃላፊው ሐሳባቸውን ሲያክሉም የሕግ ትምህርት መስጠት አለመስጠት ችግር ሆኖ እንደማያውቅ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹አብዛኛውን ችግራችን የዕውቀት ወይ የግንዛቤ ማነስ አይደለም፡፡ እኔ እዚህ ተቋም ከገባሁ ጀምሮ ተከታታይ የወንጀል ንቃት ትምህርቶች ሲሰጡ አውቃለሁ፡፡ የግንዛቤ ወይ የዕውቀት ሳይሆን ሆን ብሎ ግብ አስቀምጦ ለሆነ ፍላጎት ወይ ውጤት ወንጀል መሥራት ነው ችግራችን፡፡ የጥላቻ ንግግሮች ወንጀል መሆናቸውን፣ የጦርነት ቅስቀሳ ንግግሮች የሕግ ጥሰት መሆናቸውን ሁሉም ያውቃል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ግንዛቤ ትምህርቶችን መስጠት እንዳለበት ይታመናል፡፡ ነገር ግን ሆን ተብሎ ግደል ይህን አውድም የሚሉ ቅስቀሳዎችና ዓላማ ያነገቡ የተደራጁ ወንጀሎችን በዚያው ልክ ማስቆምም አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፤›› በማለትም ጉዳዩ ተደራጅቶ ሕግን የመጣስ እንደሆነ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ አስቀምጠውታል፡፡ በኢትዮጵያ ይብዛም ይነስ ወጣቶች የሕግ የበላይነትን መሠረታዊ ዕውቀት የጨበጠ ትውልድ ሆነው የሚያድጉበት ዕድል ቢኖርም፣ ነገር ግን በዋናነት በወጣቱ ዘንድ የተባባሰ የሕግ ጥሰት ሲፈጸም ይታያል፡፡

በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች የሕግ የበላይነት መርህ መሸርሸሩን አመላካች ሆነው ይቀርባሉ፡፡ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው ቀውሱን የፈጠረው የሕግ የበላይነት ግንዛቤ ማጠር ሳይሆን፣ ሕግን የማስከበር ሥልጣን የተሰጠው አካል ኃላፊነቱን ተገንዝቦ በተገቢው ሁኔታ አለመወጣቱ ነው ይላሉ፡፡ ይህን ሐሳብ ከሚጋሩት አንዱ የሆኑት የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ አሰፋ፣ የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ በተጨባጭ በተግባር የተተረጎመበት ጊዜ አለ ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ፡፡ የሕግ የበላይነት ሳይሆን የባለሥልጣናት የበላይነት ነው በኢትዮጵያ ያለው ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በአሁኑ ወቅት እጅግ ተባብሶ አገሪቱን አደጋ ላይ እንደጣላት ነው የሚያስረዱት፡፡ ‹‹የሕግ የበላይነት የሕግ ተፈጻሚነትን ኃይል/ደረጃ የሚያመላክት ነው፡፡ ሕጉ በትክክል በተግባር ተፈጻሚ ሲሆን ነው የሕግ የበላይነት አለ የምንለው፡፡ በእኛ አገር መንግሥታት ታሪክ ግን ሕግ ሳይሆን ግለሰቦችና ፖለቲከኞች ናቸው የሕጉም የበላይ ሆነው የምናገኛቸው፡፡ በንጉሡ ጊዜ ንጉሡ፣ በደርግ ጊዜ ደርግ፣ በኢሕአዴግም ጊዜ ኢሕአዴግ ነበሩ የበላዮች እንጂ ሕጉ አልነበረም፡፡ ‹‹እኛ አገር ያለው የሕግ የበላይነት ሳይሆን የሰዎች ከሕግ በላይ የመሆን ነው፡፡ ግለሰቦች፣ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች፣ የጎበዝ አለቆች የፈለጋቸውን የሚያደርጉበት ሥርዓት ነው የተፈጠረው፡፡ በዘር፣ በቀዬና በሃይማኖት ቡድን ፈጥረው የፈለጉትን የሚያደርጉ ኃይሎች ተበራክተዋል፡፡

‹‹ሕግ የማስከበር ኃላፊነት የመንግሥት ቀዳሚው ሥራና ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ነገር በሙሉ ቀጥሎ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡና ለደኅንነታቸው እንዳይሠጉ ማድረግ ነው የመንግሥት ተቀዳሚ ሥራ፡፡ እነ እከሌ ናቸው የችግሩ ምንጭ እያሉ ሰበብ መፍጠር አይሠራም፡፡ የሕግ የበላይነት ባለመከበሩ ምን ያላጣነው ነገር አለ? ንብረታችንን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ሁሉ እያጣን ነው፡፡ ከተማ ውስጥ እየኖርን እንኳ ከሥጋት አልወጣንም፡፡ ደኅንነታችንም ሆነ ሕይወታችን ተናግቷል፤›› በማለት የተናገሩት የሕግ ባለሙያው አቶ መንግሥቱ፣ የሕግ የበላይነት በተግባር ባለመተርጎሙ ያለውን ከባድ አደጋ ለማመላከት ሞክረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በወጣቱ በኩል ብቻ ሳይሆን በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ የሕግ ጥሰት መስፋቱ ጎልቶ ይተቻል፡፡ ከፖለቲከኞች እስከ ምሁራን፣ ከሕግ አስከባሪዎች እስከ አገልግሎት ሰጪዎች፣ በሁሉም ዘርፍ የሚፈጠረው የሕግ ጥሰት የሕግ የበላይነትን በተጨባጭ ለመተርጎም ፈተና መሆኑን ብዙዎች ያስቀምጡታል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በቶሎና በጊዜ መቀጨት ባለመቻሉ እየተባባሰ መጥቶ፣ ዛሬ የሕግና ሥርዓት መሠረት በሆኑ የእምነት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር መግባቱ ይነገርለታል፡፡ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ባለመቻሉ ኢትዮጵያውያን ለረዥም ዘመናት ጠብቀው ያቆዩትን የሃይማኖት መከባበርና መቻቻል ቀስ በቀስ ሸርሽሮ ወደ እምነት ግጭት ያዘነበሉ ያልተለመዱ ቀውሶችን በመካከላቸው እየፈጠረ መሆኑን ነው ብዙዎች በሥጋት የሚናገሩት፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ገና በጊዜ ሲያቆጠቁጥ ባለመቀጨቱና በማድበስበስ በመታለፉ፣ ዛሬ አድጎ የአገር ምሰሶ የሆኑ የእምነት ተቋማትን አናግቷል የሚለው ሐሳብ እየጎላ ነው፡፡

ይህን የሚስማሙበት የፍትሕ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አወል፣ ‹‹በፊት በዘር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በሃይማኖት እየተሞከረ ነው፡፡ ሆን ብለው በጅተውና አቅደው ይህን መሰል ወንጀል ለመፈጸም የተደራጁ ኃይሎች እዚህም እዚያም አሉ፡፡ ይህን ማስቆም ደግሞ ዋናው የፀጥታ ኃይሎች ሥራ ነው፡፡ የደኅንነት መዋቅሩ የት ቦታና በእነ ማን ወንጀሎቹ ይፈጸማሉ የሚለውን በጥልቀት አጥንቶ ዕርምጃ ይውሰድ፡፡ ያ ሲሆን እኛም ፋታ አግኝተን ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ላይ እናተኩራለን ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉ ችግሩ የደረሰበትን ደረጃና መፍትሔውን አያይዘው ያስረዳሉ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ አልቻለም የሚል ትችት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከብዙ ወገኖች ይደመጣል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) በጥር ወር በመቶ ቀናት የዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ከካቢኔ አባላት ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ደካማነት በጉልህ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹በብዙ ማስረጃዎች ልከራከራችሁ እችላለሁ እኛ ስለፍትሕ ለማውራት ብዙ ሩቅ ነን፡፡ ስለፍትሕ ለማውራት አንችልም፤›› ብለው፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ከፖሊስ ጀምሮ በየደረጃው ባሉ ዕርከኖች በገንዘብ የሚደለልና ተገቢ ፍትሕ የማይገኝበት መሆኑን በሰፊው ተችተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ክልል ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ባሉ ጊዜያት፣ በትግራይ ተወላጆች አያያዝና ፍትሕ አሰጣጥ ላይ ታይቷል ያሉትን ጉድለት ነበር እንደ አንድ ማሳያ አድርገው ያቀረቡት፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ አወል ደግሞ የፍትሕ ሥርዓቱ ችግሮች ሰፊ መሆናቸውን ነው የሚያስረዱት፡፡ ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ሲባል ብዙ ጊዜ ከስሙ ነው መሰል የመብራት፣ የውኃና ሌላም የማኅበራዊ ፍትሕ አገልግሎት ተጓደለብኝ የሚል ቅሬታ ሁሉ ነው የሚቀርብልን፡፡ ነገር ግን እኛ በቀጥታ የሚመለከተን የራሳችን ኃላፊነት አለብን፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋናው ደግሞ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ወይም ከሰላም ጋር የሚገናኘው የፍትሕ ሥራ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ደግሞ እኛ በዋናነት የምንጫወተው ሚና የወንጀል ምርመራ ሥራን መምራት፣ ምርመራው ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ይሆናል፡፡ የተመረመረው ወንጀል ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ አጥፊዎች እንዲጠየቁ ማድረግም የእኛ ሥራ ይሆናል፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ የወንጀል መከላከል ሥራዎችም ሆነ ሌሎች ሚናዎች የእኛ ኃላፊነት አይደሉም፡፡ እኛ ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ እንጂ ከመፈጸሙ በፊት ያለው ሥራ አይመለከተንም፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ነው ይህ ኃላፊነት ያለበት፡፡ ‹‹ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ትልቅ ችግር ግን ወንጀል መከላከል ላይ ሥራ አልተሠራም የሚል ነው፡፡ የፀጥታ ተቋማትና ፖሊስ ወንጀል ሊፈጸሙ የሚችሉባቸውን ጉዳዮች ቀድመው መርምረው ማስቆም እንዳለባቸው ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ወንጀል እዚህ ቦታ ሊከሰት ነው ብሎ ማስጠንቀቅም ሆነ ወንጀሉን ላስቁም ብሎ የፍትሕ ሚኒስቴር ቢንቀሳቀስ፣ በሌሎቹ የፍትሕ ተቋማት ላይ ጣልቃ መግባት ሲሆን ይህ ኃላፊነቱም አይደለም፤›› በማለት የሚያስረዱት አቶ አወል፣ ፍትሕ ሚኒስቴር በተሰጠው ኃላፊነት ላይ ብቻ ምን ሠራህ መባል አለበት ይላሉ፡፡ አቶ አወል ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት ዕርምጃ አለመወሰዱ ዋና የፍትሕ ሥርዓቱ እንቅፋት መሆኑን ከመናገር ባለፈም፣ የፍትሕ ሚኒስቴር በራሱ በኩል የተሰጠውን ሚና በሚፈለገው ልክ ለመፈጸም የአቅሙን ያህል መጣሩን ይገልጻሉ፡፡