በጋዜጣዉ voice|ET News by Dawit Atreso
በጋምቤላ ክልል መቀመጫ ጋምቤላ ከተማ በታጣቂዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል ዛሬ ማክሰኞ ንጋት አካባቢ የጀመረ ውጊያ ሲካሄድ መቆየቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ የክልሉ ፕሬስ ሴክሪተሪያት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መረጃ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር እና የሸኔ ወታደሮች በጋራ ተኩስ መክፈታቸውን ገልጧል፡፡
መንግሥት በሽብርተኝነት የሰየመውና ሸኔ ሲል የሚለው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሲል የሚጠራው ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ነው የሚባለው ኦዳ ተርቢ የተሰኘው ግለሰብ በበኩሉ በትዊተር ገጹ ሠራዊታቸው ከጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጋር በመሆን በጋምቤላ ከተማ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።ግለሰቡ አክሎም ከጋምቤላ በተጨማሪም በምዕራብ ኦሮሚያ በደምቢ ዶሎ ተመሳሳይ ወታደራዊ ዘመቻ እያደረገ መሆኑን ገልጿል። ቢቢሲ አንድ ሥማቸው ያልተገለጸ የክልሉን ከፍተኛ ባለሥልጣን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ክስተቱ በጋምቤላ ከተማ ውስጥ ማጋጠሙን አረጋግጠው፣ በዚህም የሰው ህይወት መጥፋቱንና የተጎዱ መኖራቸውን ገልጸዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የክልሉ ባለሥልጣን ቢያንስ ሁለት የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም ከታጣቂዎቹ የሦስቱ ህይወት ማለፉን ከሆስፒታል ምንጮቻቸው መረዳታቸውን ተናግረዋል።