ኢትዮጵያ ተፈናቃዮችን በሚመለከት ሕግም ሆነ ኃላፊነት የሚወስድ ተቋም የላትም ተባለ

 ethiopian human right commussion
May 2022

by Dawit Atreso

በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸም ግድያ አሳሳቢ ተብሏል

ኢትዮጵያ ቁጥሩ እየበዛ የመጣውን የተፈናቃዮች ችግር እልባት ለመስጠት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍም ሆነ ሥራውን በባለቤትነት የሚሠራ ተቋም እንደሌላት ተነገረ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ረዕቡ ግንቦት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሥር ወራት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ሲያቀርብ፣ አገሪቱ ከተፈናቃዮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሕግም ሆነ የተቋምም ማዕቀፍ እንደሌላት ተመልክቷል፡፡ በየጊዜው በግጭትና ጦርነት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን የተፈናቃይ ዜጎችን ችግር መፍታት ባለመቻሉ ብዙዎች ለረዥምና ውስብስብ ችግሮች ተዳርገዋል ተብሏል፡፡ በየጊዜው ከተፈናቃዮች አያያዝ ጋር በተገናኘ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ቅሬታ ቢቀርብም፣ የነዚህን ዜጎች ጉዳይ የሚመለከት ተቋምም ሆነ ሕግ ባለመኖሩ ችግሩን ለመፍታት አለመቻሉን ነው የኮሚሽኑ ሪፖርት ያመለከተው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት አሳሳቢና መሻሻል የሚሏቸውን ጉዳዮች አስቀምጠዋል፡፡ በጦርነትና ግጭት ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ተከታታይ ክትትል ማድረግን በተመለከተ ችግር መኖሩን ያመለከቱት ኮሚሽነሩ ‹‹በብሔር፣ በሃይማኖትና በአስተዳደር ወሰን በሚነሱ ግጭቶች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ደርሷል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የማስቆም ዋና ሚና የመንግሥት መሆኑን በማስገንዘብም ሁኔታዎች ወደነበሩበት ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለሱ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ መፈናቀልን በተመለከተ ‹‹ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ያጡና ለረዥም ጊዜ የተፈናቀሉ ዜጎች በመብዛታቸው አግባብነት ያለው ጥበቃና ድጋፍ ለመስጠት በቂ ትኩረት ተሰጥቶት የሕግ ማዕቀፍና ተቋም መፍጠር፤›› አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነትን በሚመለከት ደግሞ የመንግሥት ኃይሎች የሚፈጽሙት ከሕግ ውጪ የሆነ ግድያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአሳሳቢነት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የመንግሥት ኃይሎች የሚወስዱት ያልተመጣጠነ ኃይል፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰርና በእስር ማቆየት፣ በጋዜጠኞችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚፈጸም ተደጋጋሚ እስራት፣ እንዲሁም ብሔር ተኮር እስራት ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አጋላጭና ዕርማት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው የተቋሙን ውጤታማ ሥራዎችና ተቋማዊ ፈተናዎች በሰፊው ዘርዝረዋል፡፡ ክትትልና ምርመራን በተመለከተ በዘጠኝ ወራት 1,410 አቤቱታዎች አስተናግደናል፣ 65 ቦታዎችን ሸፍነናል፣ ከ700 ያላነሱ ቃለ መጠይቆችን አድርገናል እንዲሁም 450 ሺሕ ስደተኞች የያዙ አሥር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ክትትል አድርገናል ሲሉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽነር ራኬብ አክለውም ከ270 ባላነሱ ፖሊስ ጣቢያና ማረሚያ ቤቶች ላይ ክትትል መደረጉን የጠቀሱ ሲሆን፣ ወደ 750 አላግባብ የታሰሩ ሰዎችን ማስፈታታቸውንም አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ በአሥር ወራት ‹‹ወደ 40 የክትትል ውጤቶችን በመግለጫም ሆነ በሪፖርት መልክ ይፋ አድርገናል፤›› ያሉት ኮሚሽነሯ ነገር ግን በተፈናቃዮች ጉዳይ ላይ ያለው የሕግና የተቋም አልባነት ለሥራቸው ፈተና እንደሆነ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወደ 1.5 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚያስጠልሉ 47 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎችን በአምስት ክልሎች ክትትል አድርገናል፤›› ያሉት ኮሚሽነር ራኬብ ‹‹ሆኖም የተፈናቃዮችን ቅሬታ የሚሰማና ችግሮችን የሚፈታ ተቋም በአገሪቱ አለመኖሩ ችግር ፈጥሯል፤›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለፓርላማው የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ የተፈናቃዮችን ጉዳይ የተመለከተ ራሱን የቻለ ሕግና ተቋም እንዲበጅ ጠይቋል፡፡ ኢሰመኮ ከዚህ በተጨማሪም ሥራውን ለማስፋትና ቅርንጫፎቹን ለማብዛት እንዲረዳው ተጨማሪ በጀት ምክር ቤቱ እንዲፈቅድለት ለቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አቅርቧል፡፡